Home > About us

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነባቢ፣ ለባዊና ሕያው ነው፡፡ በዚህ ተፈጥሮአዊ ባህርይው አንዱ ሰው ከሌላው ሰው መልዕክት የሚያስተላልፍበት ልዩ ልዩ መንገዶች ሲኖሩ እነዚህም በድምጽ፣ በጽሑፍ፣ በምስል፣ በምልክት፣ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም (ተንቀሳቃሽ ምስል ወድምጽ) ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ከእግዚአብሔር በተፈጥሮው ያገኛቸውን ስጦታዎች ተጠቅሞ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ያለፈና የአሁን ጊዜ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴውን የወደፊት ዕቅዱን በቅርብና በሩቅ ለሚገኙ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ያስተላልፋል፡፡ ዘመናዊ የሆኑት ልዩ ልዩ የብዙኀን መገናኛ የሰውን ልጅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት፣ የሚኖርበትን አካባቢ መልካም ገጽታ፣ የማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ዕሴት፣ የዕድገትና የሥልጣኔ ክንውን ከአንዱ የምድር ጠርዝ ወደ ሌላው ጽንፍ በፍጥነትና በጥራት በማስተላለፍ የሰውን ልጅ ሁለተናዊ ግንኙነት በማፋጠን በአወንታዊ ገጽታቸው አርበ ሰፊዋን ዓለም በማቀራረብ ድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥልጣኔዎች መረጃዎችን ከማሰራጨት ባሻገር ዘግበው ለትውልድ በማስተላለፍም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ የዓለም መንግሥታትና የግል ተቋማት ለዚሁ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ከተጠቃሚነት ባሻገር ለዘርፉ እድገት የሚጠበቅባቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፲፱፻፰፮ ዓ/ም በፊት በሀገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ እንዲሁም በሉተራን ፌደሬሽን የብሥራተ ወንጌል፣ የምሥራች ድምጽ ይባል በነበረው የሬዲዮ መገናኛ የሰላም፣ የእምነትና የማኅበራዊ ተልእኮ ትምህርቶቿን፣ ዓመታዊ በዓላቷንና ሥርዓተ አምልኮቷን በቀጥታ ሥርጭት የማስተላለፍ ዕድል ነበራት፡፡ ይኽ እንቅስቃሴ በወታደራዊው ሥርዓተ መንግሥት ከተቋረጠ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ መልእክት በመጽሔትና በጋዜጣ ሥርጭቶች፣ በቅርቡም በመጠነኛ የድረ ገጽ ዝግጅቶች ብቻ ተወስኖ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የመገናኛ ብዙኅን አገልግሎት ሥርጭት ማቋቋም አስፈላጊነት

 • በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በዓለም መንግሥታት ድንጋጌዎች መረጃን የማግኘት መብት የሰብዓዊ መብት አካል ሲሆን በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ለፍጥረት ሁሉ ጊዜና የቦታ ሳይወስነው የማዳረስ ሀላፊነቷን ለመወጣት እንድትችል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
 • የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ቀኖና፣ ታሪክና ወቅታዊ እንቅስቃሴ ወቅቱ በፈቀደውና ትውልዱ በደረሰበት ሥልጣኔ ለምእመናን ማዳረስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
 • በመላው ዓለም ያሉ ምእመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርትና ሥርዓት ወቅታዊ ሁኔታ እንዲደርሳቸው፣ ቤተ ክርስቲያን ባልታነጸባቸውና መምህራን ባልተሰማሩባቸው አካባቢዎች፣ በሕመም ምክንያት በሆስፒታል፣ በካምፕና በማረሚያ ቤቶች ያሉ አማኞችን ለማስተማርና ለማጽናናት አስፈላጊ በመሆኑ፣
 • በመላው ዓለም ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባላት ልዩ ልዩ አስተዋጽኦቻቸውን እና በጎ አድራጎታቸውን ለቤተ ክርስቲያናቸው የማበርከት ፍላጎታቸውን በቂ መረጃ በመስጠትና እና በታማኝነት ለማስፈጸም እንዲያስችል፣
 • ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ ሁሉም አገልጋዮቿ እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ መረጃዎች በልዩ ልዩ መንገዶች እየተሰራጩ ምእመናንና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማወቅ የሚፈልጉትን ሁሉ እያደናገሩ ስለሆነ ትክክለኛ መረጃን በዘመናዊ መንገድ ማሰራጨት በማስፈለጉ፣
 • የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንታዊና ቀኖናዊ የሆኑ የዜማ፣ የቅዳሴ፣ የሰዓታት፣ የአብነት ትምህርት፣ የትርጓሜ፣ እና የመሳሰሉት የማይዳሰሱ ዘርፈ ብዙ ቅርሶች በማእከላዊነት ደረጃውንና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲሰራጩና እንዲታወቁ ለማድረግ፣
 • በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ባለው ሰላም የቱሪስትና የመንፈሳዊ ተጓጓዦች ፍሰት በመጨመሩ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኝዎችና ተሳላሚዎች ስለቤተ ክርስቲያኒቱ በቂ መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት፣
 • ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበራዊ ሥራ፣ በሰላም፣ በማኅበራዊ እድገትና ሥልጣኔ፣ ጎጅ ልማዶችን በመቅረፍ፣ ድኅነትን በመቀነስና በማጥፋት፣ በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ፣ በመሳሰሉት ያደረገችውን አስተዋጽኦና የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለማዳረስ እንዲቻል፣
 • በአንዳንድ ብዙኀን መገናኛ የሚሠራጩ መርሐ ግብሮች በሀገራችን እምነት፣ ሥነ ምግባርና ቋንቋ፣ የሚያስከትሉትን ተጽእኖዎች መቀነስና ሚዛናዊ ማድረግ በማስፈለጉ፣
 • ክርስቲያን ባልሆኑና የሃይማኖትና እምነት ነፃነት በሌለባቸው መንግሥታት ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኀንን በመጠቀም በዘርፉ ሀገሮቻቸውንና ምእመናንን ተጠቃሚ የማድረጋቸውን ልምድ በመረዳት፣

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በሀገሪቱ እና በመላው ዓለም ካሉ ሕጎችና ስምምነቶች ጋር በማጣጣም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት እንዲኖር አንድ ወጥ የሆነ ደንብና ሥርዓት በማዘጋጀት በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ ይኽውም ተግባራዊ ሁኖ ይኽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ተቋቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት

 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ ብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ማሠራጫ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአዲስ አበባ ይገኛል
 • እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከሀገሪቱ ውጭ ባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አህጉረ ስብከት ቅርንጫፍና ንኡሳን ጽ/ቤቶች ይኖሩታል፡፡
 • ዋና መሥሪያ ቤቱ በሥሩ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ ዘርፎችና ባለሙያዎች ይኖሩታል

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዋና ዓላማ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ ብዙኀን መገናኝ አገልግሎት ማሠራጫ ድርጅት ዋና ዓላማ፡-

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ አምልኮት (ቀኖናት)፣ ታሪክና ቅርስ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ የበጎ አድራጎትና ልማት፣ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች ማሳወቅ፣ ማስተማርና አወንታዊ ለውጥ ማምጣት ሲሆን ብዙኀን መገናኛን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሏት ዕሴቶች ለሰው ልጅ ድኅነት፣ ሁለተናዊ ጥቅምና ክብር፣ ለሀገር እድገት፣ ሰላምና በጎ ገጽታ የበኵሏን አስተዋጽኦ እንድታደርግ ማስቻል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዝርዝር ዓላማዎች

 • የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ለትርፍ ወይም ለጥቅም ብቻ ሳይሆን ለማሳወቅ፣ ለማስተማርና ለአወንታዊ እድገት እንዲሆኑ መሥራት፣
 • የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የቤተክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ሥርዓተ እምልኮት፣ ትውፊት፣ ታሪክና ቅርስ፣ ባሕልና ዕውቀት መሠረት ለሕዝቦች ዕድገት ያበረከተችውንና በማበርክት ላይ ያለችውን አስተዋጽኦ ማሳወቅ፣
 • የሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የቅድስና መፍለቂያ የሆኑ ገዳማት፣ አድባራት፣ የአብነት ት/ቤቶች፣ የትምህርት ተቋማት ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ አቅምና እንቅስቃሴ፣ ያላቸውን አስተዋጽኦ በማሳየት ድጋፍ፣ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግቸው ማስቻል፣
 • ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ያሉ ልዩ ልዩ የመንፈሳዊ ፣ የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት የሥራ ዘርፎችን እንቅስቃሴ ማቅረብ፣
 • በይዘታቸው የቤተክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ሥርዓትና ታሪክ መሠረት ያደረጉ ትምህርቶች፣ ምክሮች፣ ዜማዎችና ሥርዓተ አምልኮት፣ መንፈሳዊ ተውኔቶችና መልእክቶች ማቅረብ፣
 • ቤተ ክርስቲያን በሰላም፣ በማኅበራዊ ዕድገት፣ በልማት፣ በአብሮ መኖር፣ በተፈጥሮ እንክብካቤና በአካባቢ ጥበቃ፣ በጎጅ ልማዶችና ድህነት ቅነሳ ያላትን አስተምህሮና እንቅስቃሴ ማሳየት፣
 • መንፈሳዊ ዕውቀቶችን ማዳበርና፣ የኅብረተሰብን መንፈሳዊ ዕሴት የሚያሳዩ መርሐ ግብሮችን ማስተላለፍ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ተልዕኮ

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ በተሰጠው መምሪያ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ተልእኮ

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓተ አምልኮት፣ ታሪክ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልዕኮ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎቶች መፈጸምና ማስፈጸም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት መሠረታዊ አቋሞች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት በዋናነት ሃይማኖታዊ ተልዕኮን የሚፈጽም ስለሆነ፣

 • በሀገሪቱ በማንኛውም የፖለቲካ ጉዳዮችና የመንግሥት አስተዳደር ጣልቃ አይገባም፤
 • በሌሎች ሀገሮች የፖለቲካ ጉዳዮችና የመንግሥት አስተዳደር ጣልቃ አይገባም፤
 • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መሠረታዊ ትምህርቶች፣ ቀኖናትና ታሪክ ጋር የማይጣጣሙ ወይም ተቃራኒ የሆኑ መርሐ ግብሮችን አያስተላልፍም፤
 • የግለሰቦችና ኅብረቶች፣ የሌሎች የእምነት ተቋማት መብትና ክብር ተጻጻሪ የሆኑ መልእክቶችን አያሰራጭም፡፡

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት አደረጃጀትና መዋቅር

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የቤተ ክርስቲያኒቱ ይፋዊ የመገናኛ ብዙኀን ሥርጭት ድርጅት በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ መሠረት ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ዋና ዋና መዋቅሮች ይገኙበታል፤

 • የሥራ አመራር ቦርድ፣
 • ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
 • ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ/ የሰው ኃይል ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ
 • ልዩ ልዩ የሙያ ሥራ ክፍሎችና ሠራተኞች አሉት፡፡
Share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Theme developed by TouchSize - Premium WordPress Themes and Websites